በአማራ ክልል አራት ከተሞች የተጣለው የእንቅስቃሴ እገዳ ማሻሻያ ተደረገበት
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል አራት ከተሞች ተጥሎ የቆየው የእንቅስቃሴ እገዳ ማሻሻያ እንደተደረገበት የክልሉ ኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከል ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
በባህር ዳር፣ እንጂባራ፣ ቲሊሊና አዲስ ቅዳም ከተሞች ከመጋቢት 23 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተጥሎ የቆየው የተሽከርካሪም ሆነ የሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ ከዛሬ ጀምሮ ተነስቷል።
ክልከላው ሊነሳ የተቻለውም በባህርዳርከተማ እና በአዊ ዞን ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው የተለዩ 183 ሰዎችን በመለየት ክትትል ማድረግ በመቻሉ እንደሆነ ጠቅሷል።
እንዲሁም ቫይረሱ ምልክት ሳያሳይ በሰዎች ላይ ሊቆይ የሚችለው ለ14 ቀናት በመሆኑና ይህ ቀንም በመጠናቀቁ እንደሆነ አመልክቷል።
በተጨማሪም ቫይረሱ ሊያስከትል በሚችለው ችግር፣ በመተላለፊያ መንገዶችና መወሰድ
ባለባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ጠንካራ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በመከናወኑ ህዝቡም መከላከል ይችላል ተብሎ በመታመኑ ክልከላው መነሳቱን መግለጫው አብራርቷል።
ቫይረሱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ሳይጎዳ መከላከል በሚቻልበት አግባብ አሰራሮች በመዘርጋታቸው ክልከላው እንደተነሳ ያሳወቀው መግለጫው የፌዴራል መንግስት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተቀመጠው አግባብ እንደሚቀጥል ጠቅሷል።
በዚህም መሰረት ማንኛውም ተሽከርካሪ መጫን ካለበት በግማሽ ሲቀንስ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ከአንድ ሰው በላይ ማሳፈር እንደማይችል ተቀምጧል።
እንዲሁም ማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት ለቅሶ፣ ሰርግ፣ ክርስትና፣ ልደት፣ እድር፣ እቁብ እና በሌሎች ሃይማኖታዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ከአራት ሰዎች በላይ መሰባሰብ እንደማይቻል አመልክቷል።
የመንግስት ሰራተኞች ከሚያዚያ 7 2012 ጃምሮ ለቫይረሱ ስርጭት በማያጋልጥ አግባብ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በስራ ቦታቸው በመገኘት መደበኛ ስራቸውን እንደሚጀምሩም ገልጿል።
መጪው የትንስኤ በዓል ግብይትም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ መከናወን እንዳለበት ያሳሰበው መግለጫው፤ በቀጣይ በቫይረሱ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ እየተከታተለ መረጃዎችን እንደሚሰጥም ኮማንድ ፖስቱ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision