Fana: At a Speed of Life!

የባንክ ካዝናን በመስበር ገንዘብና መሳሪያ ዘርፈዋል የተባሉ ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጋገን ባንክ የረር ቅርጫፍን ካዝናን በመስበር ገንዘብና አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር ዘርፈዋል ተብለው የተከሰሱ 8 ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ አጠቃላይ ስምንት ሲሆኑ 1ኛ ተከሳሽ ገበያው ምስጋናው፣ 2ኛ እዮብ ተመስገን፣ 3ኛ የሆቴል ባለቤት ነው የተባለው ይርጋለም አድማሱ፣ 4ኛ ተሾመ ደምሴ፣ 5ኛ ሀይለማርያም መለሰ፣ 6ኛ ጥላሁን ወልዴ፣ 7ኛ ጌታሁን ተፈራ እና 8ኛ ተከሳሽ አቤል ንጉሴ ናቸው።

የቦሌ ምድብ ዐቃቤ ህግ ሁለት የወንጀል ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን በአንደኛው ክስ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ አምስት ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ነው።

በዚህም “ገበያው ምስጋናው የተባለው አንደኛ ተከሳሽ በወጋገን ባንክ የረር ቅርንጫፍ በጥበቃ ሰራተኛነት ሲሰራ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ላይ የዕለቱ ተረኛ ጥበቃ ሰራተኛን በማገት  እጅና እግሩን በገመድ በማሰርና አፉን በፕላስተር በማፈን የባንኩን የገንዘብ ካዝና በፌሮ ብረት በመስበር 409 ሺህ 172 ብር በጥሬ እንዲሁም አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር ዘርፈዋል” ሲል ዐቃቤ ህግ ጠቅሷል።

ሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ6ኛ እስከ 8ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በዚህ ክስ ከላይ የተጠቀሱ በአምስት ተከሳሾች ከወጋገን ባንክ ጃክሮስ ቅርንጫፍ ዘርፈዋል የተባለውን አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር 6ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ወልዴ ገዝቶ ለ7ኛ ተከሳሽ ለጌታሁን ተፈራ መሸጡ ተጠቅሷል።

7ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ8ኛ ተከሳሽ አቤል ንጉሴ ደላላነት መሳሪያውን ለሌላ ላልተያዘ ግለሰብ በመሸጥ በአጠቃላይ በከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ የተከሰሱ ናቸው።

በክሱ ላይ ወንጀሉ ተፈጽሟል በተባለበት ቀን የዕለቱ ተረኛ ጥበቃ አባል እጅና እግሩን በገመድ በማሰር በህይወት ይኑር አይኑር ባልተለየበት ሁኔታ የደረሰበት እንደማይታወቅ ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ነበር።

እነዚህም ተከሳሾች ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ”ወንጀሉን አልፈጸምንም” ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ስድስት ምስክሮችን በተለያዩ ቀናቶች አቅርቦ አሰምቷል።

ችሎቱ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን መርምሮ ተከሳሾቹ ገንዘብ እና አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 ጥይት ጋር በተደረገ የዝርፊያ ወንጀልን በሚመለከት ብቻ የምስክርነት ቃል መሰረት እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ ብይን ተሰጥቷል።

ወንጀሉ ተፈጽሟል በተባለበት ወቅት አንድ ተረኛ ጥበቃ አባል እጅና እግሩን በገመድ ታስሮ ተከሳሾቹ የት እንዳደረሱት እንደማይታወቅም ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ያቀረበውን ክስ በሚመለከት ግን በቀረቡ ምስክሮች ግለሰቡ ጉዳት ደርሶበት ስለመሰወሩ የሚገልጽ ማስረጃ ባለመቅረቡ ውድቅ አድርጎታል ።

ፍርድ ቤቱ ከባድ የተደራጀ የውንብድና ወንጀል የሚለውን የክስ አንቀጽ በመቀየር በውንብድና ብቻ በሚል አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

በዛሬ የችሎት ቀጠሮ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች ከማረሚያ ቤት የቀረቡ ሲሆን 6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ግን በተፈቀደላቸው የ13 ሺህ ብር ዋስትና በውጭ ሆነው በችሎት ቀርበዋል።

የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.