Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለድርቅ አደጋው መንግስት የሰጠው ምላሽ ዜጎችን ከጉዳት መታደጉን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ልክ ስራ ባይሰራ በርካታ ዜጎች ይጎዱ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በኢትዮጵያ ድርቁ ተከስቶ በርካታ ጉዳቶችን ማስከተሉን አንስተዋል፡፡

ይህ ድርቅ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር በመንግስት፣ በአጋር ድርጅቶች እንዲሁም በኢትዮጵያ ህዝብ ትብብር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባባዎች በተከሰተው ድርቅ ልክ ስራ ባይሰራም በርካታ ዜጎች ይጎዱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በመንግስት በኩል በሶስት ክልል ባሉ በ10 ዞኖች በሚገኙ 61 ወረዳዎች የቅድሚያ ቅድሚያ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል የተባሉ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ ቀርቦላቸዋል፡፡

እንዲሁም በስምንት ክልል በሚገኙ 32 ዞኖች 6 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ በደቡብ ኦሞ በ6 ወረዳዎች ለ300 ሺህ ዜጎች እርዳታ ደርሷልም ነው ያሉት ፡፡

ቦረናን በተመለከተም አካባቢው ሰፊ ቦታ እንዳለውና ችግሩ ውሃ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ያንንም ታሳቢ አድርገን እንሰራለን ነው ያሉት ፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታት እነዚህ አካባቢዎች ከተረጂነት ወደ ረጂነት እንደሚሸጋገሩም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል የትግራይ ክልልን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ምክር ቤቱ በቅርቡ የሕወሓትን የሽብር ፍረጃ እንዲነሳ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይን ህዝብ ወደ ሌላው ህዝብ ለማምጣት ምክር ቤቱ አበክሮ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ኦሮሞ እና አማራ መካከል ያሉ ሽኩቻዎች ማንንም አይጠቅሙም፣ በእርጋታ፣ በመስከን፣ በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱ ወገኖች የፈለገው ችግር ቢኖር ከመገፋፋት እና ውጥረት ይልቅ በወንድማማችነት መንፈስ ሊሰሩ ይገባል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.