Fana: At a Speed of Life!

350 ሺህ ዶላር አሽሽቷል የተባለው ተጠርጣሪ ላይ የ7 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ወደ ሀገር ይዞ የገባ በማስመሰል 350 ሺህ የአሜሪካ ዶላር አሽሽቷል የተባለው ተጠርጣሪ ላይ የሰባት ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

ክስ እንዲመሰረት ለዓቃቤ ሕግ የሰባትቀን ጊዜ የፈቀደው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ተጠርጣሪው ከጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ አውሮፕላ ማረፊያ ከሚሰራ አንድ ሰራተኛ ጋር በመመሳጠር በፈረንጆቹ ነሐሴ 15 ቀን 2019 ምንም የጉዞ ታሪክ ሳይኖረው 350 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ይዠው የገባሁት ነው በማለት  የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ሰነድ በመጠቀምና ዲክሌር በማስደረግ ዶላሩን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ በማሸሽ መጠርጠሩ ተመላክቷል፡፡

በዚህም በመንግስትና በሕዝብ  ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል መጠርጠሩን ተከትሎ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሲከናወን የቆየው ምርመራ ተጠናቋል።

መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ቀጠሮ ምርመራውን አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ገልጿል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው÷ ክስ ለመመስረቻ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ፤ የተጠርጣሪው የዋስትና መብትም ሊከበር ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

መዝገቡን የተመለከተው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ዓቃቤ ሕግ ከጠየቀው የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ውስጥ የሰባት ቀን ጊዜ ብቻ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.