ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ ያርስ በተባለው አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤል ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች

By Mikias Ayele

March 29, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ያርስ የተባለውን አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤል በመጠቀም ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ መጀመሯን አስታውቃለች፡፡

በወታደራዊ ልምምዱ ከ3 ሺህ በላይ ወታደሮች ተሳታፊ ሶሆኑ 300 ያርስ ሚሳኤል ደግሞ ጥቅም ላይ እንደሚውል አልጄዚረ የሩሲያን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ ዘግቧል።

ያርስ የተባለው ይህ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤል 12 ሺህ ኪሎ ሜትር ወይም 7 ሺህ 500 ማይልስ ርቀት ድረስ መሄድ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን በውስጡ በርካታ የኒውክሌር አረሮችን መሸከም ይችላል ተብሏል፡፡

የአሁኑ ወታደራዊ ልምምድም ሩሲያ የኒውክሌር መሳሪያ አቅሟን ለማሳየት ያለመ ነው እየተባለ ነው።

ወታደራዊ ልምምዱ በሶስት የተለያዩ ግዛቶች የሚካሄድ መሆኑንም የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመላክታል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ያርስ ባላስቲክ ሚሳኤልን ከማይደፈሩ የሞስኮው የጦር መሳሪያዎች አንዱ ለማድረግ አቅደዋል ነው የተባለው።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ በግል እና ከሌሎች ሀገራት ጋር በመጣመር በርካታ የጦር ልምምዶችን ስታደርግ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል።