ተንቀሳቃሽ የቲቢ በሽታ መመርመሪያ ክሊኒኮች ስራ ላይ ዋሉ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 6፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ተንቀሳቃሽ የቲቢ በሽታ መመርመሪያ ክሊኒኮች ስራ ላይ መዋላቸው ተገለፀ።
የጤና ሚኒስቴር የቲቢ በሽታን መመርመር የሚያስችሉ ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮችን ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ማበርከቱም ነው የታወቀው።
ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮቹ በአፋር፣ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች አገልግሎት እንደሚሰጡም ነው የተነገረው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ፥ መንግስት በ2035 ዓ.ም ከቲቢ ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን የመፍጠር ዓላማን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
ይህን እውን ለማድረግ በተለይም ከአርብቶ አደር አካባቢዎች የኑሮ ሁኔታ ጋር የሚስማማ የቲቢ ምርመራና የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ከዚህ አንጻር የተዘጋጁት ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለውን ችግር በመፍታት ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
በክሊኒኮቹ ዘመናዊ ላቦራቶሪና ሌሎች ቲቢን መመርመር የሚያስችሉ ግብዓቶችን እንደያዙም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።
ክሊኒኮቹ የተገዙት ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መሆኑንም ገለጸዋል።
ክሊኒኮቹ በዋናነት ከጸሃይ ብርሃን ሃይልን እንደሚጠቀሙ ገልጸው፥ ጀነሬተርና የመስመር ኤሌክትሪክን እንደአስፈላጊነቱ በአማራጭነት መጠቀም ይችላሉም ተብሏል።
ድንገት ቢበላሹ ጥገና መስጠት የሚያችሉ ባለሙያዎች ቀደም ብሎ ማሰልጠን እንደተቻለም ነው ያብራሩት።
አገልግሎቱ አዲስ እንደመሆኑ የክልል ጤና ቢሮዎችና ትግበራው የሚካሄድባቸው ዞንና ወረዳዎች ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል ።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!