Fana: At a Speed of Life!

ቻይና የታይዋን መሪ በአሜሪካ ጉብኝት እንዳያደርጉ አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የታይዋን መሪ ጻይ ኢንግ ዌን በአሜሪካ ሊያደርጉ ያሰቡትን ጉብኝት እንዳያደርጉ አስጠንቅቃለች፡፡

ቤጂንግ የታይዋን መሪ ከአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ኬቪን ማካርቲ ጋር ከተገናኙ የአፀፋ እርምጃዎችን እንደምትወስድ አስጠንቅቃለቸ፡፡

ጻይ በዛሬው እለት ለ10 ቀናት የስራ ጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚያቀኑ ሲሆን፥ በአሜሪካ ከሚኖራቸው ቆይታ በተጨማሪ ወደ ቤሊዝ እና ጓቴማላ እንደሚያቀኑም አር ቲ ዘግቧል።

የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ኬቨን ማካርቲ በበኩላቸው ከቻይና በኩል ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ከታይዋኗ መሪ ጋር እንደሚገናኙ ተናግረዋል።

መሪዋ ከአፈ-ጉባኤ ማካርቲ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት የገለጹት ነገር ባይኖርም÷ የታይዋን ባለስልጣናት ግን በካሊፎርኒያ ቆይታቸው ከሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች ጋር እንደሚመክሩ ለፋይናንሺያል ታይምስ መናገራቸውን ዘገባው አስታውሷል።

ታይዋን የሉዓላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ቻይና የቁጣ ምላሽን ላለማስተናገድ ስትል ሁለቱ ወገኖች እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት ለህዝብ ይፋ እንደማያደርጉም ዘገባው አውስቷል።

በቻይና የታይዋን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ዡ ፌንግሊያን የታይዋኗ መሪ ከአፈ ጉባኤው ጋር ከተገናኙ የአንድ ቻይና ፖሊሲን የሚጥስ ጠብ አጫሪ ድርጊት ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አያይዘውም ድርጊቱ የቻይናን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስና በታይዋን የባህር ወሽመጥ ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርስ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የቀድሞዋ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በታይዋን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ቻይና በምላሹ በታይዋን የባህርና የአየር ክልል ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ የሚታወስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.