የሀገር ውስጥ ዜና

በኃይል አቅርቦት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት ማበረታቻዎች እንደሚያቀርብ ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

March 29, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኃይል አቅርቦት ላይ ለሚሰማሩ የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች መንግስት ከታክስ ጋር የተያያዙ ማበረታቻዎችን ጨምሮ መሬት በነጻ እስከ ማቅረብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ያደርጋል ተባለ፡፡

በበርሊን ከተማ የኃይል አማራጭ ላይ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ÷ የኢነርጂ ሃብት ልማት በመንግስት ወጪ ብቻ ስለማይሸፈን የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ይሻል፡፡

እንደ ሀገር ከውሃ ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ÷ በፀሐይ ኃይል፣ በንፋስና በአነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮች ቢሳተፉ በፈረንጆቹ 2030 ሁሉንም ዜጎች የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡

በኃይል አቅርቦት ላይ ለሚሰማሩ የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች መንግስት ከታክስ ጋር የተያያዙ ማበረታቻዎችን ጨምሮ መሬት በነጻ እስከ ማቅረብ ድረስ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ያደርጋል ማታውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡