Fana: At a Speed of Life!

የቀይ ቀበሮዎችን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅና ለመከታተል የሚያግዝ ”ፖላር” የተሰኘ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቀይ ቀበሮዎችን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅና ለመከታተል የሚያግዝ ”ፖላር” የተሰኘ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሩን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቋል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቀይ ቀበሮዎች ጥበቃ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጌታቸው አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቴክኖሎጂው በፓርኩ ያሉ ቀይ ቀበሮዎችን የአኗኗርና የጤና ሁኔታ እንዲሁም ስነ-ተዋልዶና እንቅስቃሴያቸውን ለመከታተል የሚያግዝ ነው።

ቴክኖሎጂው ከዚህ ቀደም በፓርኩ ስለቀይ ቀበሮዎች መረጃ ለማሰባሰብ በባለሙያዎች ይካሄድ የነበረውን አድካሚ የእግር ጉዞ በማስቀረት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሳይንሳዊ መረጃ ለማሰባሰብ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት ቴክኖሎጂው በቀይ ቀበሮዎች አንገት ላይ የሚታሰር ሲሆን በሳተላይት አማካኝነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚያስችል ነው።

ባለፉት ሶስት ሳምንታት በተደረገ እንቅስቃሴ በአራት ቀይ ቀበሮዎች አንገት ላይ ቴክኖሎጂው ታስሮ ሥራው መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀይ ቀበሮዎቹ አንገት ላይ የተገጠመው ቴክኖሎጂ በአንድ ላይ የሚኖሩ እስከ 40 የሚደርሱ የቀይ ቀበሮ የቤተሰብ አባላትን ለመከታታል እንደሚረዳም ገልጸዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ቴክኖሎጂው የተገጠመለት ቀይ ቀበሮ በቀን ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደተጓዘና የት ቦታ እንደሚገኝ እንዲሁም በህይወት ስለመኖሩና ሲሞትም የት ቦታ ሞቶ እንዳለ መረጃ የሚጠቁም ነው።

“ቴክኖሎጂው ቀይ ቀበሮዎቹ ያሉበትን ቦታ መጠቆም ከዚህ ቀደም ጎብኚዎች ቀበሮዎቹን ፈልጎ ለማየት የሚደርስባቸውን እንግልት ያስቀራል” ያሉት ደግሞ የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዛናው ከፍያለው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ቁጥራቸው 90 የሚደርሱ ቀይ ቀበሮዎች የሚገኙ ሲሆን ከ20 ዓመት በፊት ቁጥራቸው 20 ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.