Fana: At a Speed of Life!

እምነትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እምነትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ ሰላምና ልማት ስራዎች ላይ ከሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
 
የቢሮው ሃላፊ ሊዲያ ግርማ÷ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በንግግር መፈታት ያለባቸው የውስጥ ጉዳዮች ወደ ውጭ እየወጡ አጀንዳ ሲሆኑ እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡
 
እምነትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ ከተማዋን ለማወክ ከውስጥና ከውጭ ሚዲያን ጨምሮ በማስተባበር የሚደረጉ በርካታ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
 
ቤተ -እምነቶች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ከሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅሮች ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚገባቸው ማስገንዘባቸውን የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ÷ሃይማኖቶች የተመሰረቱበት ዋና ዓላማ ሰላም በመሆኑ ለሰላም መረጋገጥ እና የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ሚናን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
 
የእምነት አባቶችም በቤተ እምነቶች ላይ በአንዳንድ አካላት የሚሰነዘሩ ግጭት ቀስቃሽ ተግባራትን ለሀገርና ለከተማዋ ሰላምና ደህንነት ሲባል ማስቆም እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.