የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ወደተሟላ ሰላም ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እየሰጠው ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Feven Bishaw

March 30, 2023

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ወደተሟላ ሰላም ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እየሰጠው መሆኑን አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ አለም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የሰላም ስራዎች በብዙ መልኩ ድጋፍ እየተቸራቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የበይነ መንግስታት ድርጅቶች ለሰላም ሂደቱ ያላቸውን በጎ ዕይታ መሰረት በማድረግ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የህወሓት ከሽብርተኛ ድርጅትነት መነሳትና የጊዜያዊ አስተደዳር ማቋቋም ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን ያሳዩ እና የመንግስትን ቁርጠኝነት ያንፀባረቁ በመሆናቸው የበለጠ ተስፋ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆነዋል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በንግግር ለመፍታት የተጀመረው ጥረት በበጎ መታየቱ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

እዲሁም የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችና የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ጅማሮዎችም በመልካም ሁኔታ ተነስተዋል፡፡

የፖለቲካ፣ የሰላምና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተመጋግበው እየቀጠሉ መሆኑን አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አንድ ዓመት ባስቆጠረው ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ 125 ሺህ ዜጎች ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ጎረቤት ሀገራት የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው እንዲፈቱም ኢትዮጵያ የበኩሏን እያደረገች መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

በሀብታሙ ተ/ስላሴ