የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቀን የሚያመርተውን የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን መጠን ወደ 20 ሺህ ከፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዲስትሪዎች ወቅታዊውን ሁኔታ ከግሞት አስገብተው የሰራተኞቻቸውን ድህንነት በጠበቀ መልኩ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ እንዳሉት፥ በፓርኩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በርካታ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል።
በፓርኩ በጨርቃ ጨርቅ የተሰማሩ ባለሀብቶች ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የመከላከሉን ስራን የህክምና ቁሳቁስ በማምረት የድርሻቸውን መወጣት መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።
እነዚህ ባለሀብቶች የማስክ እና የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን በማምረት በገበያው ያለውን እጥረት ለመፍታት አላማ አድርገው ነው ወደ ስራ የገቡት ብለዋል ስራ አስኪያጁ።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ድርጅቶች በቀን 10 ሺህ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን እያመረቱ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
አሁን ላይ በሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ የሚገኙ ድርጅቶች በቀን የሚያመርቱትን የአፍ መሸፈኛ ጭምብል መጠን ወደ 20 ሺህ ከፍ ማድረጋቸውን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ አስታውቀዋል።
በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክም በተመሳሳይ ለሰራተኞች ደህንነት ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ስራ አስኪያጀ አቶ አህመድ ሰይድ ይናገራሉ።
በፓርኩ የሚገኙ የውጭ ዜጎች የጉዞ ታሪክ ያላቸው በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን ያነሱት ስራ አስኪያጁ፥ አካላዊ አርቀተን በመጠበቅ እና እጅን ቶሎ ቶሎ በመታጠብ ቫይረሱን ለመከላከል በጥብቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሸን ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ ደርቤ ደበሌ በበኩላቸው፥ በፓርኮቹ በሚገኙ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትም እየተከናወነ ይገኛል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ደግሞ የህክምና ቁሳቁስ ምርት መጀመሩን የተናገሩት ሀላፊው፥ በቀን 20 ሺህ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል እያመረተ ይገኛል ብለዋል።
ፓርኩ የአፍ መሸፈኛን በጥራት በማምረት በቀን የምርት መጠኑን ወደ 50 ሺህ የማድረስ እቅድ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል ።
በሀይለኢየሱስ መኮንን
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision