Fana: At a Speed of Life!

በለውጡ ሂደት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል – ብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምሥት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ ለዜጎች የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ ሥኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ÷ ኢትዮጵያ በቅድመ 2010 ዓ.ም በማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በርካታ ፈተናዎች ገጥመዋት በቁልቁለት ጉዞ ላይ እንደነበረች አስታውሰዋል።

በተለይ ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የፕሮጀክቶች መጓተትን ጨምሮ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚጣሱበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት የታፈነበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ጭላንጭል ጠፍቶ የነበረበት አጋጣሚ እንደነበርም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

የዜግነት ዲፕሎማሲ የተገፋበት፣ የሀገር ጥቅም ቅድሚያ የማይሰጥበት፣ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተዛባ ግንኙነት የነበረበት ሀገርና ህዝብን የሚጎዳ አካሄድም እንደነበርም ገልጸዋል።

በእነዚህ እና በሌሎችም ተደራራቢ ችግሮች ኢትዮጵያ በቁልቁለት ጉዞ ላይ ትገኝ ነበር ብለዋል አቶ አደም።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ግን ባለፉት አምሥት ዓመታት በርካታ ውስብስብ ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት ለዜጎች የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በሂደቱ በርካታ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች ቢያጋጥሙም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ በተለያዩ መስኮች ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን አብራርተዋል።

በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ አካታችና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሥርዓት በመከተል የተሳካ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማሥፋትም የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ተደርገው ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ማኖር ተችሏል ነው ያሉት።

ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ ስልትም በኢኮኖሚው መስክ ለአብነት የዕዳ ጫናን በማቃለልና ምርታማነትን በማሳደግ የላቀ አፈፃፀም መመዝገቡን አንስተው፤ በተለይም በስንዴ ልማት፣ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ የተገኙትን ውጤቶች ጠቅሰዋል።

የቱሪዝም ዐቅምን የመጠቀም፣ በሌማት ቱርፋት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ የተመዘገበው ስኬትም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በፖለቲካው መስክ የሐሳብ ብዝኃነት እንዲከበር፣ ሥልጣን በሀሳብ ልዕልና እንዲያዝ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረው በ6ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ የታየውን ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደትም አንስተዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ የትብብር ግንኙነትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተል የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የተጀመሩ ስኬታማ ሥራዎችን በማስቀጠል ፈተናዎችን ተጋፍጦ በማሸነፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት የሚሠራ መሆኑን አቶ አደም አረጋግጠዋል።

የተቋማት ግንባታና የዴሞክራሲ ባህልን ማጠናከር፣ ምርታማነትን መጨመር፣ ሌብነትና ጽንፈኝነትን መታገል፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በቀጣይም ቁልፍ ሥራዎች ሆነው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር፣ አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን መሥራትና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሥራ ላይ ውሎ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በማድረግ ሂደት የመንግስት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.