Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ፡፡

የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ወጥና አስተማማኝ የሀገሪቷ ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት ሥርዓት በመዘርጋት እና የተመዝጋቢዎችን መረጃ በመያዝ የዲጂታል መታወቂያ አጠቃቀም ስርዓትን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው የማድረግ ጥቅም እንዳለው በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተብራርቷል፡፡

መታወቂያውን በመጠቀም በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር ስርዓት እንዲዘረጋና የተሳለጠ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር አመቺ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም ተመላክቷል፡፡

አዋጁ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት አፅድቋል።

ምክር ቤቱም የውሳኔ ሃሳብ ሪፖርቱን ካዳመጠ በኋላ የብድር ስምምነቱን አዋጅ ቁጥር 1285/2015 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

የብድር ስምምነቱ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክትን በማስፈፀምና የመሬት ልማት ስራዎችን ለመስራት፣ ዘመናዊ የመሬት አያያዝን ለማስፈን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል፡፡

ስምምነቱ የተራቆቱ መሬቶችን ለማልማት፣ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ስራዎችን ለማጠናከር እና የመሬት ምርትና ምርታማነት እድገትን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ገቢ እና አኗኗር ለማሻሻል ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.