Fana: At a Speed of Life!

ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዟል የተባለው ተጠርጣሪ ከትዳር አጋሩ ጋር ፍርድ ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍርድ ቤት ክርክር ላይ የሚገኝ የመሬት ጉዳይን እንዲቋረጥ አስደርጋለው በማለት ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዟል የተባለው ተጠርጣሪ ከትዳር አጋሩ ጋር ፍርድ ቤት ቀረበ።

ተጠርጣሪውን ከትዳር አጋሩ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት ያቀረበው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ነው።

በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታየው ተጠርጣሪዎች 1ኛ ተጠርጣሪ ሳሙኤል ታደሰ እና 2ኛ ተጠርጣሪ የትዳር አጋሩ ወይዘሮ ቤተልየም እስክንድር ናቸው፡፡

1ኛ ተጠርጣሪ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ የሚገኝ የመሬት ጉዳይን እንዲቋረጥ አስደርጋለው በማለት ከሌሎች በዘርፉ ላይ ከሚሰሩ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር ሁለት ሚሊየን ብር ጉቦ እንዲከፈለው ድርድር አድርጓል ሲል መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አብራርቷል።

በድርድሩ መነሻ ተጠርጣሪው አስቀድሞ 350 ሺህ ብር ጉቦ መቀበሉን መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ/ምደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ የ80 ሺህ ብር ቼክና 50 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ ጉቦ ሲቀበል በጥቆማ እጅ ከፍንጅ መያዙን ለችሎቱ አብራርቷል።

ፖሊስ 2ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ገንዘብና ንብረት በማሸሽ ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር መዋሏን ለችሎቱ አስርድቷል።

መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪውን የስልክ ግንኙነት በሚመለከተው አካል ምርመራ ለማስደረግ ፣የምስክር ቃል ለመቀበል እንዲሁም ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ማስረጃ አሰባስቦ ለመቅረብ የ14 ቀን የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ በበኩሉ ÷1ኛ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሲውል በጠቋሚዎች እግሩ ላይ ድብደባ እንደተፈጸመበት ለችሎቱ አስረድቷል።

”ከመንግስት ተቋማት የሚሰበሰቡ ማስረጃዎችን ተጠርጣሪው የማጥፋት አቅም ስለማይኖራቸው ማስረጃ ለማሰባሰብ ተብሎ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አደለም ”ሲል ጠበቃው ተከራክሯል።

ተጠርጣሪው ነጋዴ መሆናቸውን የጠቀሰው ጠበቃው የሚያስተዳድሩትን ንብረት ትተው መታሰራቸውን ገልጿል።

የትዳር አጋር የሆኑት ሁለቱም ተጠርጣሪዎቹ ሁለት ህጻናት ልጆች እንዳሏቸው እና ህጻናቶቹን ትተው መታሰራቸውን በመጠቆም የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቋል።

2ኛ ተጠርጣሪ ወይዘሮ ቤተልየም በበኩሏ ÷በቁጥጥር ስር በዋለችበት ዕለት ባለቤቷ ቀኑን ሙሉ በመጥፋቱ ስታፈላልገው ውላ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በመኖሪያ ቤቷ እንዳለች በፖሊስ መያዟን አስረድታለች።

በዚህ በተያዘችበት ዕለት ነዳጅ ለመሙላት ብቻ 4 ሺህ ብር ከኤቲ ኤም ማውጣቷን የገለጸች ሲሆን÷ ከዚህ ውጪ ምንም ያሸሸሁት ንብረትም ሆነ ገንዘብ የለም በማለት ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርታለች።

የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉበት ሰዓት መቼና የት ቦታ እንደሆነ ለማረጋገጥ ለመርማሪ ፖሊስ ጥያቄ አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ 1ኛ ተጠርጣሪ በድርድሩ መነሻ ገንዘብ ሲቀበሉ በደረሰ ጥቆማ መነሻ በክትትል የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው እንደተነገረው አብራርቷል።

2ኛ ተጠርጣሪን በተመለከተም ንብረትና ገንዘብ ሲያሸሹ ይዘናቸዋል ተብሎ እንደተገለጸለት መልስ ሰጥቷል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን የተመለከቱት ዳኛ 1ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ብቻ መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ከጠየቀው የ14 ቀን ውስጥ የሰባት ቀን የምርመራ ጊዜን ፈቅደዋል።

የአንደኛ የትዳር አጋር የሆኑትን 2ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ግን ቤት ውስጥ ህጻን ልጆች ጥለው መታሰራቸውን ተከትሎ የህጻናቶችን መብት ከግምት ውስጥ በማስገባት የ10 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ከስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተላልፏል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.