Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ የተበላሸ በርካታ ቴምር መጋዝን ውስጥ ተከማችቶ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ንጽህናውን ያልጠበቀ እና የተበላሸ በርካታ ቴምር መጋዝን ውስጥ ተከማችቶ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
 
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ታይዋን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የግለሰብ መኖሪያ ግቢ ውስጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡።
 
ግለሰቦቹ በመኖሪያ ግቢያቸው በሚገኝ መጋዘን ውስጥ የተበላሸና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል በርካታ ቴምር ንፅህና በጎደለው ሁኔታ አስቀምጠው ለአትራፊ ነጋዴዎች በፌስታል አሽገው ከሸጡላቸው በኋላ ቴምሩ የተበላሸ መሆኑን የተገነዘቡት ገዢዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ሊያዙ ችለዋል፡፡
 
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የእፎይታ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከፍ/ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማወጣት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ግቢ በሚገኘው መጋዘን ውስጥ ባደረገው ፍተሻ መጥፎ ጠረን ያለው እና የተበላሸ በርካታ ቴምር ተከማችቶ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
 
የወረዳ 10 አስተዳደር የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃብቱ መካ በበኩላቸው÷ በቁጥጥር ስር የዋለው ቴምር ወደ ህብረተሰቡ ቢሰራጭ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
 
ከተጠርጣሪዎቹ የገዙትን የተበላሸ ቴምር ለህዝብ ሳይሸጡ እና የግል ጥቅም ሳያጓጓቸው ለሰዎች ጤና በማሰብ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠታቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡
 
ጊዜና ወቅትን እየጠበቁ ሕገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ነጋዴዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች ከሕግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.