Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ እና ተጓዳኝ መርሐ ግብር ከ880 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ የመጀመሪያ ዙር ሽያጭ እና በአንድ ወር ውስጥ ከሚከናወኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች ከ880 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕዝብ ተሳትፎ እና አደረጃጀት አማካሪ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር)÷ 10 ሺህ በአማርኛ 1 ሺህ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የታተሙ 11 ሺህ መጽሐፍት መድረሱን ጠቅሰው፥ ሁሉም በሽያጭ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መጽሐፉን ለሽያጭ ከማቅረብ ባሻገር በጥቅሙና ፋይዳው ላይ ተመስርቶ እንዲሸጥ፣ እንዲተዋወቅ እና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ እንዲሁም በየደረጃው ለሚገኘው ማሕበረሰብ የአስተሳሰብ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ስላለው ለሐሳብ መገንቢያ እንዲውል ይሠራል ብለዋል፡፡

መጽሐፉ ለልማት አንድ አቅም እንዲሆን በክልሉ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች እንዲካሄዱ መታቀዱን እና በዚህም ባለሃብቶች፣ ተቋማት፣ ታዋቂ ሰዎች እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ነው ያሉት፡፡

ገቢው ለፋሲል ግንብ ጥገና፣ ማስዋቢያ፣ ማልሚያ እንደሚውል ጠቁመው ለዚህ በጎ ዓላማ የክልሉ ሕዝብ በመጽሐፉ ግዥ እና በገቢ ማሰባሰቢያዎቹ በንቃት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል፡፡

ከ11 ሺህ መጽሐፍት ቀጥታ ሽያጭ 4 ሚሊየን 950 ሺህ ብር እንዲሁም ከገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች 875 ሚሊየን በአጠቃላይ ከ880 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው የተናገሩት።

እስካሁን 1 መጽሐፍ 500 ሺህ ብር የገዛ ተቋም መኖሩንም አመላክተዋል፡፡

ከመጋቢት 14 ቀን ጀምሮ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ለአንድ ወር እደሚቆይም አስረድተዋል፡፡

ለግንባታ ሥራው ሁለት ጥናቶች መጠናታቸውን ጠቁመው÷ ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደው የመጀመሪያው ጥናት ውጤት በወጪ ደረጃ እስከ 500 ሚሊየን ብር በጊዜ ረገድ ከ1 ዓመት ተኩል እስከ 2 ዓመት እንደሚወስድ ማመላከቱንም ነው የገለጹት።

ከአንድ ዓመት በፊት የተጠናው ሁለተኛው የጥናት ውጤት ደግሞ እስከ 745 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ እና ከ1 ዓመት እስከ 1 ዓመት ከ8 ወር ባለው ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ማመላከቱንም አስረድተዋል።

የሚቀድመው ገንዘብ ማሰባሰቡ መሆኑን ገልጸው ጥናቶች ከተጠኑ ስለቆዩ እና የዋጋ ሁኔታው እየጨመረ ስለሆነ እንደሁኔታው አዲስ ጥናት ሊካሄድ እንደሚችልም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.