Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያዊው ጠፈርተኛ ሰርጌ ሰቨርቺኮቭ ልምዱን ለኢትዮጵያውያን አካፈለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያዊው ጠፈርተኛ ሰርጌ ሰቨርቺኮቭ በህዋ ሳይንስ ያካበተውን እውቀት እና ልምድ ለኢትዮጵያ ምሁራን እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አጋርቷል፡፡

የሩሲያን የህዋ ሳይንስ መልካም ልምድ መቅሰም የሚያስችል የልምድ ልውውጥ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

መርሐ ግብሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ፣ በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በአዲስ አበባ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ምሁራን እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በልምድ ልውውጡ ተካፍለዋል፡፡

የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚዳንት ደረጄ ይልማ (ዶ/ር) የልምድ ልውውጡ በተለይም ለተማሪዎች ከፍተኛ መነሳሳት ይፈጠራል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሞስኮ ኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ከተለያዩ የሩሲያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የልምድ ልውውጡ የእርስበርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እና ለጋራ ግብ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡

የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ÷ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗ አስረድተዋል፡፡

ለተጀመረው ስራም የሩሲያ ልምድ እና አጋዥነት ከፍተኛ ሚና እደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

የጠፈርተኛው ልምድ ማጋራትም ኢትዮጵያ ነገ በርካታ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ እንድታፈራ ያነቃቃል ብለዋል።

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.