Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋን ታሪካዊነት የሚመጥንና ወደ ቱሪዝም ማዕከልነቷ የመመለስ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋን ታሪካዊነት የሚመጥንና ወደ ቀድሞ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ማዕከልነቷ የመመለስ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው የከተማዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ተናግረዋል፡፡

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ጁሃር ከድር በሰጡት መግለጫ ከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ ያደረገው ተግባር የሕብረተሰቡን መሰረታዊ ችግሮች መለየትና የተለየ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ሊጠናቀቁ የሚገባቸው ፕሮጀክቶን አጣርቶ ወደ ስራ ማስገባት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በዚህም በቤት ልማት ዘርፍ 300 ቤቶች ተጠናቀው ለሕብረተሰቡ በእጣ ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል። የመንገድ፣ የጤና ተቋማት እና የትምህርት ቤቶች ግንባታም በአስተዳደሩ ትኩረት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

የነዋሪዎቿ ዋነኛ ፍላጎት ለሆነው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በቤት ልማት ዘርፍ 10 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ከንቲባው አብራርተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ በኩልም በዋናነት ህዝቡን የሰላሙ ዘብ በማድረግ በቅንጅት ድሬዳዋን ከወንጀል የፀዳች የቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ስራ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

በቀጣይ በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንና የተለያዩ አይነት ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በ70 ሚሊየን ብር ግዢያቸው የተፈፀሙትን የሲ.ሲ.ቲቪ ካሜራዎች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በቅርቡ መትከል እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

ከተማዋን ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ከማድረግ ባሻገር ግንባታቸው የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ድሬዳዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መታቀዱንም የከተማዋ ከንቲባ ማስታወቃቸውን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.