Fana: At a Speed of Life!

ለግድቡ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ ሊጠናከር ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረተሰቡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድቡ ያለውን ጽኑ ድጋፍ በሚመጥን ደረጃ የማስተባበር ስራን ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ ሊጠናከር ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

በ12ኛው ዓመት ዋዜማ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሳባ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የስድስት ወራት አፈፃፀም ተገምግሞ አስተያየት እና የቀጣይ ስራ አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል፡፡

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በታላቅ ንቅናቄያችን “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” በሚል ወኔ የተረባረብንበት ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ከተጀመረ እነሆ 12 አመታት ሆነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

12 የጥረት እና የስኬት ብሎም የፈተና ጉዞ የታየባቸውን አመታት አሳልፈን በስተመጨረሻ የድል ዘመናት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት።

በዚህ ጉዞ ከሁሉ በላይ ህዝባችን በእውቀቱ፣ በችሎታው፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ሳይሰሰት ለታላቁ የባንዴራ ፕሮጀክት አስተዋጽኦ አድርጓል ያሉት አቶ ደመቀ÷ በየደረጃው ያለው አመራርም ወደር የለሽ ርብርብ ማድረጉን አውስተዋል።

በህዝባዊ ተሳትፎም ሆነ በመሬት ላይ ያለው የፕሮጀክቱ አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፥ ይሁንና ኅብረተሰቡ ለግድቡ ያለውን ፅኑ ድጋፍ በሚመጥን ደረጃ የማስተባበር ስራን ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ ሊጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከአረንጓዴ አሻራ ስራ ጋር በማያያዝ የተፋሰስ ልማቱን እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው ይገባልም ነው ያሉት።

ግድባችን በተለያዩ አካላት የሚነሳበትን የጥርጣሬ እና ስጋት አጀንዳ ሁሉ መሬት ላይ በሚታዩ ክንውኖች በተጨባጭ እያከሸፈ በተቃራኒው የተፋሰሱ ሀገራትን ይበልጥ በጥቅም የሚያስተሳስር መሆኑ ታይቷል ብለዋል።

አቶ ደመቀ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስም የታላቁ ግድባችን መሠረት ለተጣለበት 12ኛ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በታላቅ ርብርብ የማጠናቀቂያውን ድል እንደምናሳካውም እምነቴ ፅኑ ነው ሲሉ መግለጻቸውንም የጽህፈት ቤታቸው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.