በቀጣዮቹ 3 ወራት ከ7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም ድረስ 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ለ2015/16 የምርት ዘመን 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈፅሟል።
እስካለፈው ሳምንት ድረስም 5 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ መድረሱን ገልፀዋል።
ከዚህ ውስጥም 4 ነጥብ 5 ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ወደ ተለያዩ የክልል ማዕከላዊ መጋዘኖች የማጓጓዝ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
እስከ ሰኔ ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት አገልግሎት ላይ እንዲውል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።
ማዳበሪያው ሞሮኮን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የተገዛ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የማዳበሪያውን ግዥ እና የማጓጓዣውን ጨምሮ 64 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።
በዮሐንስ ደርበው