Fana: At a Speed of Life!

ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊየን ዶላር በላይ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊየን ዶላር በላይ አጸደቀ፡፡

የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ሪታ ሮይና ሌሎች የስራ አመራር ቦርድ አባላት ባለፉት አራት ቀናት በኢትዮጵያ የፕሮግራም ግምገማ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ለሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሮግራም ከ630 ሚሊየን ዶላር በላይ ማጽደቁን ሚኒስትሯ አመላክተዋል።

የጸደቀው ገንዘብ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የብድር አገልግሎት ለማቅረብ፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በስራ ፈጣሪነት አስተሳሰብ ለመቅረጽ የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም ገንዘቡ ለስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለተለያዩ ተግባራት ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚውል ነው ብለዋል።

ፋውንዴሽኑ አካታችና ፍትሐዊ ዓለም ለመፍጠር፣ ትምህርትን ለማስፋፋት፣ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና የፋይናንስ አካታችነትን የማስተዋወቅ ተልዕኮ ያለው መሆኑን ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት።

በወጣቶች የፈጠራ ችሎታ እና ስራ ፈጣሪነት አምኖ የበርካቶችን ሕልም ለመፍታት ፋውንዴሽኑ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.