Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፋሲለደስ ጥንታዊ ቤተ-መንግስትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የፋሲለደስ ጥንታዊ ቤተ-መንግስትን ጎበኙ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷”በዚህ ስፍራ አባቶቻችን የሰሩት እጅግ አስደናቂ ጥበብና የእጅ ስራ ይታያል” ብለዋል፡፡

“ፋሲለደስ፣ አክሱም፣ ላሊበላን እና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶችን ስናይ በእጦት እሳቤ ያልተያዙ፣ አቅም ፣ ዕውቀትና ጥበብን ካለበት ማምጣት፤ ማሰናሰን፣ መደመር የሚችሉ አባቶች እንደነበሩን ያሳያል” ብለዋል፡፡

“ፋሲለደስ ሁሉም ዲዛይኖቹ የሚያሳየው የተገለጠላቸው፣ የማይታየውን ማየት የሚችሉ ሰዎች እንደነበሩም ነው ብለዋል፡፡

በቤተ መንግስቱ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበሩ ሙያዎች እና ስራዎች ተንፀባርቀዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ሊቃውንቶች ወደዚህ ስፍራ መጥተው ስራው ላይ ተሳትፈዋል፤ ድሮ በጋራ የሌለው ካለው አምጥቶ ያማረ የላቀ ስራ መስራት ነበረም ነው ያሉት፡፡

እዚህ ቦታ ላይ ያየነው የተደመረ ጭንቅላት ውጤት ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ያን በቅጡ መገንዘብ እና ጠቀሜታውን አውቆና አጉልቶ መጠቀም ላይ ውስንነት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ አመለካከት፣ የቋንቋ እና የእምነት ልዩነት ሊኖረን ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የፋሲል ቤተመንግሥት ግን ሃብታችን ነው፤ ልንጠብቀው፤ ለትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የመደመር መፅሃፍ ሽያጭ ለዚሁ ቅርስ ጥገና እንዲውል የመደረጉ ዓላማም “መስራት እንኳ ባንችል ጥበቡ ገብቶን ጠግነነው ለትውልድ ማሸጋገር ይኖርብናል” የሚል እሳቤ ስላለ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ለዚህም ከህዝባችን ጋር በትብብር እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፋሲል ቤተመንግሥትንም አምሮ ለትውልድ እንደሚሸጋገር ያላቸውንም ዕምነት ገልፀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.