አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅን ከብሔራዊ ባንክ ዋጋ በላይ በሚገዙ ሕገ-ወጥ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
በርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በክልሉ መንጌ ወረዳ ወርቅ የሚመረትባቸውን አካባቢዎች የጎበኘ ሲሆን÷ የቀጣይ አቅጣጫም አስቀምጧል።
አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት ÷ በክልሉ ከዚህ ቀደም የተሻለ የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ ይገባ እንደነበር አስታውሰው አሁን ሕገ-ወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች በመበራከታቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ምርት ቀንሷል ብለዋል።
መንግስት ወርቅን በሕገ-ወጥ መንገድ ከብሔራዊ ባንክ ዋጋ በላይ በሚገዙ ግለሰቦች፣ ማኅበራት፣ ምርት በሚደብቁ አምራቾች እና ሌሎች ሕገ-ወጥ አካላት ላይ የተጠናከረ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ነው ያሉት፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የ22ኛ ክፍለ-ጦር ዋና አዛዥ ሌ/ጀኔራል ሠይፈ አንጌ በበኩላቸው÷በሕገ-ወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን ለመቆጣጠር በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ዘመቻ ይካሄዳል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡