ግንባታቸው ተጀምሮ የቆሙ መንገዶች እንደገና መጀመር እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጀምረው የቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ እንደገና መጀመር እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጀምረው የቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የቡድኑ አስተባባሪ አቶ ተሾመ ዋለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ ቡድኑ በምልከታው ተጀምረው የቆሙ የመንገድ ሥራዎችንና በየመንገዱ የቆሙ ማሽኖችን ተመልክቷል፡፡
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተወያይተው ችግሮችን በመለየትና መፍትሔ በማስቀመጥ ሥራውን ማስጀመር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶችን ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለማስጀመር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የአሶሳ አካባቢ የፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በአጭር ጊዜ የመንገድ ፕሮጀክቶቹን መከታተል እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡