Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የሚመረተው የወርቅ ምርት ህግን ተከትሎ ወደብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በትኩረት መስራት ይገባል – አቶ አሻድሊ ሃሰን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚመረተው የወርቅ ምርት ህግን ተከትሎ ወደብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ተናገሩ፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን ለመቆጣጠር በክልሉ ከሚገኙ ወርቅ አምራችች እና አዘዋዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይቱ ላይ በመከላከያ ሠራዊት የ22ኛ ክፍለ-ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሠይፈ አንጌን ጨምሮ የክልልና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተገኝተዋል።
 
አቶ አሻድሊ ሀሰን በክልሉ እየተመረተ ያለው ወርቅ አየጨመረ ቢሆንም ምርቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ብሔራዊ እየገባ አለመሆኑን አንስተዋል።
 
ወርቅን ከብሔራዊ ባንክ ዋጋ በላይ የሚገዙ ህገ-ወጥ አካላት መበራከታቸውን ጠቅሰው÷ እነዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ ለመጉዳት ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
 
በክልሉ የሚመረተው የወርቅ ምርት ሙሉ በሙሉ ህግን ተከትሎ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
 
ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት የጋራ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ በማንሳትም መንግስት ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።
 
በመከላከያ ሠራዊት የ22ኛ ክፍለ-ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ሠይፈ አንጌ ወደ ባንክ የሚገባው የወርቅ ምርት መጠን መቀነሱ ሁሉንም ሊያሳስበው እንደሚገባ ገልጸው÷ ድርጊቱ ሀገር እና ህዝብን ለመጉዳት ፍላጎት ባላቸው በተደራጁ ህገ-ወጦች የሚፈጸም መሆኑን አስረድተዋል።
 
ጉዳዩ የሀገር ኢኮኖሚ ህልውና ጉዳይ ነው ነው ያሉት ዋና አዛዡ÷ ሀብቱ ህግና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ ወደብሔራዊ ባንክ መግባት አለበት ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
 
ወርቅ አምራች እና አዘዋዋሪዎች የወርቅ ምርትን ወደ ብሔራዊ በማስገባት ራሳቸውንና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚገባ ጠቁመው ችግሩ የማይታረም ከሆነ ወደ እርምጃ እንደሚገባም ገልጸዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.