Fana: At a Speed of Life!

የጎርጎራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬን እድልና የነገ ሕልም ደምሮ የያዘ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎርጎራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬን እድልና የነገ ሕልም ደምሮ የያዘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት አካል በሆነው ጎርጎራ ጉብኝት አድርገዋል።

ፕሮጀክቱ ከሦስት ወራት በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸው÷ “ጎርጎራ ውስጥ ታሪካችን፣ እድላችንና ሕልማችን አለ” ብለዋል።

“ትናንት ታሪካችን ነው፤ ዛሬ እድልና ነገ ደግሞ በምናብ የምናየው ሕልማችን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎርጎራ ሦስቱን ቁልፍ ጉዳዮች አጣምሮ መያዙን ገልጸዋል።

የጎርጎራ ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ መጠበቅ ባለመቻሉ ምክንያት ያለውን “ግርማና መስኅብ እያጣ እንደነበር” ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ አማካኝነት ታሪካዊ ስፍራውን ዳግም እንዲወለድና እንዲታደስ በማድረግ ወደ ነበረበት ክብር መመለስ ብቻ ሳይሆን ልቆ መታየትን አሳይተናል ነው ያሉት፡፡

በጎርጎራ ፕሮጀክት የተከናወነው ስራ የትውልድ መደመርን ያሳየ ነው ብለዋ ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

“ጎርጎራ ትናንት፣ ዛሬና ነገን ያስተሳሰረ ድንቅ ስራ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ኢትዮጵያ አምራና በልጽጋ የምትታይበት ቦታ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ታሪካዊ ከመሆኑ ውጪ ጥራት፣ ብዛትና ቴክኖሎጂን በሚገባ ያስተሳሰረ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

“ጎርጎራ ትውልድ በታሪክ ውስጥ ሊሞላው የሚገባውንና የጎደለውን ሞልቶ እንዲሁም የነበረንን ማነጽና ማላቅ እንደሚቻል የታየበት፤ የኢትዮጵያን ተስፋዎች፣ ሕልሞችና የምኞታችንን ልክ ያመላከትንበት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያውያን ጎርጎራን መጎብኘትና ሌሎች እንዲጎበኙት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

የትኛውም ጎብኚ ጎርጎራን በማየት ያለ ምንም አስረጂ የኢትዮጵያን ታሪክ መማር፣ የኢትዮጵያን ልክ ለማወቅና የኢትዮጵያን ሕልም ለመረዳት እንደሚችል ተናግረዋል።

ጎርጎራ ለትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ስራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ጎርጎራን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች ውበት እንዲታይና እንዲጎላ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ወደ ትግበራ የሚገባው “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬ እድልና የነገ ሕልም በሚያሳይ መልኩ የቱሪዝም ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን ብዙ እምቅ የቱሪስት ሀብቶች ፈልቅቆ በማውጣትና በመጠቀም ለትውልድ የሚሸጋገር ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስገነዘቡት።

“ያደጉ ሀገራት የእድገት ጫፍ ላይ ደርሰው ሐሳባቸው እያረጀ መጥቷል፤ ኢትዮጵያ እያደገች ነው ወደ ነበርንበት ብቻ ሳይሆን ከዛ ባሻገር ወደ መታደስና ሕዳሴ እየመጣች ነው” ብለዋል።

ትውልዱ ይሄንን በመገንዘብ ያማረና ለትውልድ የሚያሸጋገር ስራ በየአካበቢው እንዲሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.