Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን በዛሬው እለት በሶስት ዙር በረራ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ተመላሾቹ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት ÷በውጭ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ ከመጋቢት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ከሳዐዲ አረቢያ የገቡትን ጨምሮ እስከ አሁን ባለው ሂደትም 131 ሺህ ዜጎች መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

ዜጎች በአገር ውስጥ ሰርተው እንዲለወጡ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው ያሉት አምባሳደር ብርቱካን በውጭ አገራት ለስራ መሰማራት የሚሹ ዜጎች ህጋዊውን መንገድ ብቻ መከተል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከስደት የተመለሱ ዜጎችን ወደ ማህበረሰቡ የማቀላለልና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.