Fana: At a Speed of Life!

በሚያዝያ ወር ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወቅቶች የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል – ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዩ ሚያዝያ ወር ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወቅቶች የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሚኖረው ከባድ ዝናብ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

ከመጋቢት ወር መግቢያ ጀምሮ ለተዘሩ ቡቃያዎችና በተለያየ እድገት ላይ ለሚገኙ አዝመራዎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎች ተስማሚ የአየር ጸባይ እንደሚኖርም ገልጿል።

የሚያዝያ ወር የአየር ጸባይ በሀገሪቱ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ፣ በደጋማው አካባቢ በሚዘሩ ሰብሎችም ሆነ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ለእንስሳት የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።

እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የበልግ ወቅት እርሻ ዘግይተው ለጀመሩና የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት ለሚጠባበቁ አርሶ አደሮች አመቺ የሆነ የአየር ሁኔታ ሰለሚኖር ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አስገንዝቧል።

ከበልግ ወቅት ዝናብ የመዋዥቅ ባህሪ አንጻር ተከታታይ ደረቃማ ቀናት በወሩ ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል የተነበየው ኢንስቲትዩቱ÷ እርጥበት አጠር የሆኑ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን የማሰባሰብ ስራ በትኩረት ሊያከናውኑ እንደሚገባ ገልጿል።

በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና በደቡብ የሀገሩቱ ክፍሎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በትንበያው ተመላክታል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊፈጠር ስለሚችል ጎርፍን አስቀድሞ መከላከል ላይ ከወዲሁ የወሃ መፋሰሻዎችን ማጽዳትና ማስተካካል እንደሚገባም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.