ከ163 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጋቢት 15 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ክትትል ከ163 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ፡፡
109 ነጥብ 8 ሚሊየን የገቢ እና 52 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የወጪ ዕቃዎች ናቸው በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተያዙት፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ÷ አዋሽ፣ ሞያሌ እና ድሬዳዋ ቅርንጫፎች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቅደም ተከተላቸውም÷ 41 ሚሊየን፣ 15 ነጥብ 6 ሚሊየን እና 15 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ይዘዋል፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች መካከል÷ አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡