Fana: At a Speed of Life!

በርካቶችን ለጉዳት የሚዳርገው የፒራሚድ ንግድ በኢትዮጵያ በድጋሚ የመስፋፋት ጉዳይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትኬር የተሰኘ ድርጅት በፒራሚድ ንግድ መሰማራቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያ የፒራሚድ ንግድ ስርአትን በህግ ብትከለክልም የተለያዩ ድርጅቶች በተለያየ ጊዜ በዚህ ህገወጥ ተግባር በበርካቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወቃል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ምርመራ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ኢትኬር የተባለ ድርጅት በዚህ የንግድ ስርአት አባላትን እየመለመለ መሆኑን ደርሶበታል።

ብዙዎችን ለጉዳት በዳረገው ህገወጥ የንግድ መንገድ ተሰማርተው የቆዩት ቲያንስን የመሰሉ ድርጅቶች የህግ እርምጃ ተወስዶባቸው ከድርጊታቸው እንዲገቱ ቢደረጉም ሌላ ድርጅት በዚህ ተግባር ላይ መሰማራቱን የሚያመለክት መረጃ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ደርሶታል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የደረሰውን መረጃ ለማጣራት የጋዜጠኞች ቡድን አቋቁሞ ጉዳዩን በመመርመር እንደተገነዘበው ኢትኬር የተሰኘው ድርጅት በፒራሚድ የንግድ ስርአት (ፒራሚድ ስኪም) ላይ መሰማራቱን በመረጃ ደርሶበታል።

ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁለት ቢሮዎቹ ተመዝጋቢ መስለው ባደረጉት ቆይታም የፒራሚድ ንግዱ አባል እንዲሆኑ የተለያዩ ማግባቢያዎች ቀርበውላቸዋል።

ድርጅቱን ከተቀላቀሉ በቀን 23 ሺህ 400 ብር በአንድ አካውንት ብቻ እንደሚያገኙም ተነግሯቸዋል።

በኢትኬር ህግ አንድ ሰው የሶስት አካውንት ባለቤት መሆን እንደሚችል እና በዚህም በቀን 70 ሺህ 200 ብር ድረስ ማግኘት የሚችል ሲሆን ይህም በወር ሲሰላ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ይደርሳል።

ጉዳት የደረሰባቸው ባለታሪክ ግን ይህ የፒራሚድ ስኪም “በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ” ቁማር ነው ይላሉ።

ምርመራውን የቀጠለው የጋዜጠኞች ቡድን አባላትም ቴሌግራምን በመሰሉ ማህበራዊ መገናኛዎች የሚደረጉ ማግባባቶችና መደለያ በሚቀርብባቸው ሁነቶች መሳተፍ ጀምረዋል።

በዚህም ብር በአቋራጭ የሚገኝበት መንገድ ይሰበካል፣ አባላትን አምጡና በትርፍ ተንበሽበሹ የሚሉ ማግባቢያዎች ቀርበው ግንኙነቱ እያደገ መጥቶ በስልክም ማውራት ቀጥሏል።

ይህ በፒራሚድ ንግድ ስርአት የሚሳተፈው ድርጅት በንግድ ፈቃዱ ላይ 500 ሺህ ብር ካፒታል እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን በአንደኛ አመቱ 20 መኪናዎችን በፒራሚድ ስልቱ ለበረቱ አባላቱ እንደሚሸልም ይገልጻል።

እንዴት ለሚለው ጥያቄም “ሁሉንም ገንዘባችን ስላላስመዘገብን” የሚል ክርክር ያቀርባል።

በድርጅቱ ሰነድ የማኔጅመንት ቡድን አባላት ተብሎ ስማቸው የተጠቀሰው አንድ ኢትዮጵያዊ እና ሁለት የውጭ ዜጎች መሆናቸውንም በተደረገው ማጣራት ማወቅ ተችሏል።

ይህ ኢትኬር የተሰኘ በፒራሚድ ንግድ ላይ የተሰማራ ድርጅት የውበት መጠበቂያና ተጨማሪ ምግቦችን የማምረት ፈቃድ ያለው ሲሆን አባላትን ሲመለምል ይሄንን በሌሎች ዘርፎች የተሰጠውን ፈቃድ ማሳያ በማድረግ ነው።

ሆኖም የፒራሚድ ንግድ በተከለከለበት አዋጅ እንደተመላከተው ከዚህ ቀደም የነበሩ በፒራሚድ ንግድ የተሰማሩ ድርጅቶች ያደርጉ እንደነበረው የሽያጭ ስርአቱ ፒራሚድን የተከተለ ነው።

አንድ ሰው አባል ይሆናል፣ ያ አባል ሌሎች አባላትን ይመለምላል፣ የተመለመሉት አባላትም እንዲሁ ሌሎችን ያመጣሉ እናም በዚህ መልኩ የንግድ መረቡ እየተስፋፋ ፒራሚድ ቅርጽ ይይዛል።

በዚህም ተጠቃሚ የሚሆኑት ከላይ ያሉት ጥቂቶች ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን ጉዳት ይደርስባቸዋል።

ድርጅቱ አባላቱን የሚመድበውም በኮከብ ሲሆን ይህ በፒራሚድ ስኪም ላይ የተሰማራ ድርጅት በርካታ አባላትን በመመልመል ላይ ይገኛል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጎንደር፣ ደሴ፣ ሀዋሳና ሌሎች ከተሞችም ቅርንጫፎች መክፈቱን ለመረዳት ተችሏል።

ለመሆኑ የድርጅቱ ሌሎች ተግባራት ምንድናቸው? የትኞቹን ህጎች ተላለፈ? የሚሰራው ህገወጥነትስ? የሚለውን በቀጣይ ዘገባ እንመለስበታልን።

በፋና የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.