Fana: At a Speed of Life!

በሕገወጥ መንገድ መድሐኒቶችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መድሐኒት የመሸጥ ሆነ የማከፋፈል ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገወጥ መንገድ መድሐኒቶችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ክትትል ነው ሁለት ግለሰቦች ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው ዳማስ በተሰኘ መኪና ልዩ ልዩ መድሃኒቶችን ጭነው ሲንቀሳቀሱ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው እፎይታ የገበያ ማዕከል አካባቢ እጅ ከፍንጅ የተያዙት፡፡

በዚህም የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ግለሰቦቹ ልዩ ልዩ መድሐኒቶችን ከድሬዳዋ ከተማ በሕገወጥ መንገድ ማምጣታቸውን እና መድሐኒት የመሸጥም ሆነ የማዘዋወር ፍቃድ የሌላቸው መሆኑ እንደተረጋገጠም ፖሊስ ገልጿል፡፡

ደርጊቱ ህግን ተከትለው በሚሰሩ የንግዱ ማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫናን የሚያስከትል መሆኑ መገለፁን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይ ደግሞ ከመድሃኒት ጋር ተያይዞ የሚፈፀም ህገወጥ ድርጊት በሰዎች ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በእጅጉ የከፋ ስለሆነ መሰል ህገወጥ ድርጊቶችን የማጋለጥ ተግባራት ሊጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.