Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በ317 ቦታዎች የአደጋ ተጋላጭነት ስጋት መኖሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በ180 ቦታዎች የጎርፍ አደጋ፣ በ104 ቦታዎች የመሬት መንሸራተት እንዲሁም በ33 ቦታዎች የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት እንዳለ የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ሰሞኑን የዝናብ ወቅት በመሆኑ እና መጪው የክረምት ወቅት በመሆኑ በመዲናዋ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለጎርፍ እና ለሌሎች ችግሮች ተጋላጭ ሆነው በስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ይገልፃሉ፡፡

የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ካሉባቸው አካባቢዎች ውስጥም ቦሌ እና የካ ክፍለ ከተማ ይጠቀሳሉ፡፡

በአካባቢዎቹ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ነዋሪዎች መጪው ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስጋቱ እንዳየለባቸው እና የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ምክትል ኮሚሽነር ይከፈለው ወልደመስቀል ኮሚሽኑ በመዲናዋ የአደጋ የተጋላጭነት ጥናት ስራ መስራቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል፡፡

በዚህም በመዲናዋ በ180 ቦታዎች የጎርፍ አደጋ፣በ104 ቦታዎች የመሬት መንሸራተት እንዲሁም በ33 ቦታዎች የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት እንዳለ ነው የተናገሩት።

ከ180 የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎች ውስጥ 284 የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው በአንድ ቦታ ከአንድ በላይ ችግር ስለሚያጋጥም ከቦታው የችግሩ ቁጥር ከፍ ማለቱን አመላክተዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም የተጋላጭነት ጥናት ሲካሄድ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ዝቅተኛ ተጋላጭ የሆነ ተብሎ መለየቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 168 የሚሆኑት ከፍተኛ ተጋላጭ ሲሆኑ ከእነሱ ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ከመጪው ክረምት በፊት ችግሩ መፈታት የሚገባቸው 55 የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎች ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡

በዚህም ቅድመ የመከላከል ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንና አደጋ ከደረሰ በኋላም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.