የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ትርፋማነት አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በተሰራ ስራ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ስር የሚገኙ ተቋማት ከኪሳራ እንዲወጡ እና ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉ ተገለፀ፡፡
በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ብቻ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ስር የሚገኙ 9 ተቋማት ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰባቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ከ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ በማትረፍ ከእጥፍ በላይ እድገት ማስመዝገባቸው ተመላክቷል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ኃይለሚካኤል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገቢው ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል። የተቋማቱ የተጣራ ትርፍም ከእጥፍ በላይ ማደግ ችሏል ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ከውጭ ምንዛሬ አንጻር 300 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት አቅደው 185 ሚሊየን ዶላር ማግኘት እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም የግብአት እጥረትና መሰል ምክንያቶችን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከዘጠኙ የልማት ድርጅቶች አንዳንዶቹ በኪሳራ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶቹ ደግሞ ትርፋማነታቸው ከሚጠበቀው ያነሰ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በተሰራ የለውጥ ስራ ተቋማቱ ከኪሳራ እንዲወጡ አለፍ ሲልም ትርፋማ እምንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
የልማት ድርጅቶቹ ከሚያገኙት ትርፍ ለመንግስት የትርፍ ድርሻ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ የብሄራዊ እንሰሳት ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ኢኒስቲትዩት ብቻ በያዝነው አመት መክፈል ከሚገባቸው 139 ሚሊየን ብር መክፈል የቻሉት 26 ሚሊየን ብር ብቻ መሆኑም ታውቋል፡፡
ከሶስቱ ውጪ ያሉት ስድስት ተቋማት የመንግስት ትርፍ ድርሻ እየከፈሉ አለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
ተቋማቱ የተጠራቀመባቸውን እዳ አቃለው ወደ ጤናማ የፋይናንስ ስርአት ሲመጡ የመንግስት ትርፍ ድርሻን እንዲከፍሉ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡
ይህን በቋሚነት የመቆጣጠርና የመከታተል ስራም እየተሰራ ነው ተብሏል።
በኃይለኢየሱስ ስዩም