Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጭው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት እንደገለጹት÷ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ለቀጣዩ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚውል ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ለመጭው ክረምት በክልል ደረጃ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኝ ለማፍላት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከሚዘጋጀተው 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኝ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ቢሊየኑን ለመትከል መታቀዱን ጠቁመው÷ እስካሁን በተሰራ ስራም ከ800 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለቆጠራ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

ከችግኝ ዝግጅቱ ጎን ለጎንም የመትከያ ቦታ የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በቀጣዩ ክረምት ችግኞቹን ከ201 ሺህ ሄክታር በላይ ለመትከል መታቀዱን ያነሱት አቶ እስመለዓለም÷ እስካሁንም 187 ሺህ ሄክታር ቦታ መለየቱን አስረድተዋል።

ለመትከያ አገልግሎት ለሚውሉ ቦታዎች የካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ስራ እተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.