Fana: At a Speed of Life!

የአንድ አውራ ዶሮ ጉዳይ ጎረቤታም ናይጄሪያዊያንን ፍርድ ቤት ወስዷል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜናዊ ናይጄሪያ የጎረቤት አውራ ዶሮ እንቅልፍ ረብሾኛል በሚል ቅሬታ ማቅረቡን ተክትሎ የናይጀሪያ ፍርድ ቤት አውራ ዶሮው እንዲታረድ ትዕዛዝ መስጠቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ትዕዛዙን የሰጡት በናይጀሪያ የፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሀሊማ ዋሊ ሲሆኑ የአውራ ዶሮው ባላቤት ማላም የሱፍ አውራ ዶሮው እየጮኸ ጎሬቤት በመረበሹ እስከ መጭው አርብ ድረስ እንዲታረድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

የአውራ ዶሮው ባለቤት ማላም የሱፍ በበኩሉ አውራ ዶሮውን “ጉድ ፍራይደይ” ወይም ቅዱስ አርብ ለተባለው የክርስቲያኖች በዓል ቤተሰቦቹን ለመጋበዝ ዶሮው መገዛቱን በመግለፅ በዓሉ እስከሚደርስ ጊዜ አንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የፍርድ ቤቱ ዳኛ የአቶ ማላም የሱፍን ጥያቄ የተቀበሉ ሲሆን አውራ ዶሮው ግን በጎረቤት አካባቢ ድርሽ እንዳይል እና እየጮኸ ነዋሪዎችን እንዳይረብሽ ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል፡፡

አቶ የሱፍም ቃል በገባው መሰረት በመጭው አርብ አውራ ዶሮውን አርዶ እንዲበላ አሊያ ግን ከፍርድ ቤቱ ቅጣት እንደሚጠበቀው ዳኛዋ ሀሊማ ዋሊ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ይህን ይበል እንጂ በአብዛኞቹ የናይጄሪያ አካባቢዎች ከብቶችን እና ዶሮዎችን ቤት ውስጥ ማቆየት እንደ ወንጀል አይቆጠርም ሲል ኤ ኤፍ ፒን ጠቅሶ የኡጋንዳው ዳይሊ ሞኒተር ጋዜጣ  ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.