Fana: At a Speed of Life!

ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች ጤናማ እንስሳትን በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ወደ ውጪ ሀገር ለሚልኩ ቄራዎች የሚሸጡበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑ ተመለከተ፡፡

የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አሥራት ጤራ (ዶ/ር) በዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚገኙ አርብቶና አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ እንስሳቱን ለቄራዎች እንዲያቀርቡ በማስተሳሰር ቄራዎችም በቀላሉ ወደ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከግብይት ሰንሰለት ጋር ያሉትን ተግዳሮቶች በመፍታት ከአቅማቸው በታች እያቀረቡ ያሉ ቄራዎችን ለማገዝ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡

ሥራው እየተከናወነ ያለው ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት፣ ከኅብረት ሥራ ኮሚሽን እንዲሁም ከክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች፣ ግብርና ቢሮ እና ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ሦስት ግብረ ኃይል ወደ ደቡብ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክላስተር አቅንቶ ከአካባቢዎቹ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በመወያየት የእንስሳት ልየታ፣ የማኅበራቱን አቅምና ፍላጎት እንዲሁም የገበያ ማዕከላትና የማቆያ ቦታ ዝግጁነትን የማረጋገጥ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የመስክ ሥራው እስከ ቀጣዩ ሣምንት መጀመሪያ እንደሚጠናቀቅ እና ከበዓል በኋላም ከቄራዎች ጋር የውል መፈራረም ይከናወናል ነው ያሉት፡፡

ይህም የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር፣ መስፈርቶቹን የሚያሟሉ እንስሳት ለቄራዎቹ እንዲቀርቡ በማድረግ፣ የአርብቶና አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሳደግን መሰረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአረባብ ዘዴ ኋላቀርነት፣ ገበያ ተኮር የአመራረት ብሎም የአረባብ ስልት ባለመከተል፣ በሻጭ እና ሸማች መካከል ያለ የተንዛዛ የግብይት ሥርዓት፣ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ የእንስሳት ዝውውር፣ በየኬላዎች በሚደረገው ተደራራቢ ቀረጥና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሃብት ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ይነሳል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከእንስሳትና እንስሳት ውጤቶች ከ137 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት እየተሠራ ነው፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.