Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡

የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎች እና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከእነ ማስረጃው በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት እንዲሁም ሰባት ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችን ከእነማስረጃው በቁጥጥር ሥር ውለዋል ነው ያለው።

ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዕድናትን በማውጣት በኮንትሮባንድ ከሀገር እንደሚያወጡ ደርሸበታለሁም ብሏል የጋራ ግብረ-ኃይሉ፡፡

በተጨማሪም በህገ-ወጥ መንገድ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ተባባሪ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ላይ እያደረገ ያለው ጠንካራ ክትትል በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቆማ መሠረት በተካሄደው ጠንካራ ክትትልና ዘመቻ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር የጋራ ግብረ-ኃይሉ አመስግኗል፡፡

በየትኛውም አካባቢ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.