Fana: At a Speed of Life!

ለ2015/2016 የምርት ዘመን ከ15 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2015/2016 የምርት ዘመን ከ15 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
 
በመግለጫቸውም፥ በ2015 የበልግ ወቅት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ከዚህም 24 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ እስካሁንም ግምሽ ያህሉ መሬት መታረሱን ተናግረዋል፡፡
 
ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱንም ጠቅሰዋል፡፡
 
በዚህ መሰረትም 12 ነጥበ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን ነው የገለጹት፡፡
 
በተጨማሪም ከባለፈው ዓመት የከረመ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል መኖሩን ጠቁመው፥ በአጠቃላይ ለምርት ዘመኑ 15 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
 
ከእርሻ ስራው ውስጥ 92 በመቶ የሚሆነው አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች የሚፈጸም መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያብራሩት፡፡
 
በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ እና ጤፍ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሚመረቱ ምርቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ለበልግ ምርት 36 ሺህ 199 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለስርጭት ዝግጁ መደረጉን ጠቅሰው፥ ለበጋ መስኖ ስንዴም 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ እየተሰራጨ ነው ብለዋል፡፡
 
አሁን ላይ ያለውን ከፍተኛ የበልግ ዝናብ በአግባቡ መጠቀም እና በመስኖ ለምተው የደረሱ ሰብሎችን ያለ ብክነት መሰብሰብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
 
በሌላ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናትን በህገ ወጥ መንገድ በማምረት ስራ ተሰማርተው የነበሩ የውጭ ዜጎች እና ተባባሪያቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አንስተዋል፡፡
 
እነዚህ አካላት የጉዞ ሰነድ፣ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሁም የሥራ ፈቃድ እንደሌላቸው ነው የገለጹት፡፡
 
በዚህም በጋምቤላ 45 የውጭ ሀገር ዜጎች እና 3 ኢትዮጵያውያን ከነ ኤግዚቢታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
 
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 47 የውጭ ዜጎች፣ 9 ሃላፊነታቸው የተወሰነ ኩባንያዎች እንዲሁም 7 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል፡፡፡
 
በአካባቢዎቹ የነበረው የሰላም መደፍረስ ለህገ ወጥ ስራዎቹ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.