Fana: At a Speed of Life!

የአቶ ሽመልስ አብዲሳን ስም በመጠቀም ህገወጥ የሲሚንቶ አከፋፋይ ማህበር በማደራጀት የተከሰሱ ግለሰቦች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ስም በመጠቀም ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና ህገወጥ የሲሚንቶ አከፋፋይ ማህበር በማደራጀት ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ ስምንት ተከሳሾች እስከ 20 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሶች 1ኛ የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ባለሙያ የሆነው አዲሱ አንጋሳ ዴሬቻ፣ 2ኛ የ1ኛ ተከሳሽ ወንድም የሆነው ታደለ አንጋሳ ዴሬቻ፣ 3ኛ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወርቁ ጫላ፣ 7ኛ ተከሳሽ ሚሊዮን ቶሎሳ፣ 9ኛ ተከሳሽ ከተማ ጉቱ፣ 19ኛ ተከሳሽ የሆለታ አስተዳደር የፋይናንስ ሰራተኛ የሆነችው ወይዘሮ ገነት ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቡ ባርኔሮ ቅርንጫፍ ሰራተኞች የሆኑት 12ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች እየሩሳሌም ጌታሁን እና ካሳሁን ኩምሳ ናቸው።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሙስና ጉዳዮች ዴይሬክቶሬት በተከሳሾች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ አምስት ተደራራቢ የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቧል።

ይኸውም አንደኛው ክስ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት 2ኛ ተከሳሽን እና ሌሎች ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦችን በአባልነት በማደራጀት በህገወጥ መንገድ በሀሰተኛ ማስረጃ በዱከም ከተማ በቶክቻ ቀበሌ ሚልኪ የሲሚንቶ አቅራቢ ማህበር ማቋቋማቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ በተቋቋመ ህገወጥ የሲሚንቶ አከፋፋይ ማህበር ውስጥ 2ኛ ተከሳሽና የሆለታ አስተዳደር ፋይናንስ ባለሙያ የሆነችውን 10ኛ ተከሳሽን አባል በማድረግ 3ኛ፣ 7ኛ፣ እና 9ኛ ተከሳሶች ከዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሚንቶ እንዲወስዱ በመተባበር በአጠቃላይ የሲሚንቶ ምዝበራ በመፈጸም የክልሉን መንግስት የታክስ ገቢ ማሳጣታቸው ተዘርዝሯል።

በዚህም 29 ሚሊየን 655 ሺህ 565 ብር ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዐቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

ሁለተኛው ክስ በ1ኛ፣ በ2ኛ፣ በ12ኛ እና በ13ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ ክስ 1ኛ ተከሳሽ የኦሮሚያ የደህንነት ተቋም አባል ሆኖ እንደሚሰራ እየታወቀ 2ኛ ተከሳሽ ጋር በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቡ ባርኔሮ ቅርንጫፍ ሰራተኛ የሆኑት 12ኛ እና 13 ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር ሌላ ለ2ኛ ጊዜ ባቋቋሙት ሚልኪ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል ስም በሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም የባንክ ሒሳብ በመክፈት 12 ሚሊየን 843 ሺህ 700 ብር ምዝበራ መፈጸማቸው በክሱ ተገልጿል።

4ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ ማለትም የኦሮሚያ የደህንነት ባለሙያ የነበረው አዲሱ አንጋሳ ዴሬሳ የተባለው ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን፥ ተከሳሹ ማንነቱን በመደበቅ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ሽመልስ አብዲሳን ስም በመጠቀም እና ወንድማቸው ነኝ በማለት ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት በቡራዩ ከተማ የኢንቨስትመንት መሬት አሰጣለሁ እያለ በማታለል ከግል ባለሀብት 2 ሚሊየን ብር በመጠየቅ እና 60 ሺህ ብር አስቀድሞ በመቀበል የማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙን ዐቃቤ ህግ ገልጿል።

ይኸው ተከሳሽ በ5ኛ ክስ ላይ በቀረበበት የወንጀል ክስ ደግሞ በኦሮሚያ ደህንነት ቢሮ የ10ኛ ክፍል ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ 350 ሺህ ብር ገንዘብ መውሰዱ ተጠቅሶ ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ የመጠቀም ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

ተከሳሾቹ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና ንዑስ ቁጥር 2 በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሰባት ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ግን በቁጥጥር ስር ባለመዋሉ ምክንያት ክሱ በሌለበት መቀጠል ይችላል ሲል ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በሌለበት እንዲቀጥል ብይን ሰጥቶ ነበር።

ክሱ በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ሰባቱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ጠቅሰው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል።

ዐቃቤ ህግ ክሱ ሊሻሻል አይገባም ሲል ምላሹን በፅሁፍ አቅርቦ ፍርድ ቤቱም መርምሮ ክሱ ሊሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ የለውም ሲል ውድቅ አድርጓል።

ክሱ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ወንጀሉ ለመፈጸሙ የሚያስረዱ 27 ምስክሮችን በማስቆጠር እንዲሰሙለት ጠይቆ፥ ፍርድ ቤቱ ከ27 የዐቃቤ ህግ ምስክሮች መካከል የ22 ምስክሮችን ቃል አዳምጧል።

የምስክር ቃል ከመረመረ በኋላ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተከሳሾች በተከሰሱበት አንቀጽ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን ሚሊዮን ቶሎሳ እና ከተማ ጉቱ የተባሉ ተከሳሾች ግን የቀረበባቸው አንቀጽ ተቀይሮ በአንቀጽ 420 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት ጥፋተኛ ተብለዋል።

የሆለታ አስተዳደር ሰራተኛ ናት የተባለችው ተከሳሽ ገነት ታደሰን ደግሞ በሙስና አዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 የነበረውን በንዑስ ቁጥር 1 በመቀየር የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባታል።

የባንክ ሰራተኛ ናቸው የተባሉት 11ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ማለትም እየሩሳሌም ጌታሁን እና ካሳሁን ኩምሳ የተከሰሱበት አንቀጽ ተቀይሮ በወንጀል ህግ አንቀጽ 703 ንዑስ ቁጥር 3 መሰረት ጥፋተኛ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን የቅጣት ማክበጃ አስተያየትና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ ፍርድ ቤቱ የኦሮሚያ ደህንነት ባለሙያ የነበረውን 1ኛ ተከሳሽ አዲሱ አንጋሳ ጥፋተኛ በተባለበት አንቀጽ በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በ200 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

2ኛ ተከሳሽ ታደለ አንጋሳ በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ 3ኛ ተከሳሽ የክልሉ የቀድሞ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወርቁ ጫላን ደግሞ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

ቀሪ ተከሳሾችን ደግሞ ከአንድ አመት ከ2 ወራት ቀላል እስራትና ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

ተከሳሾቹ እጅ ላይ የተገኘ 8 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ እና ከ565 ሺህ ብር በላይ ገንዘብም እንዲወረስ ታዟል።

በዚህ መዝገብ ተከሰው ነገር ግን ሳይያዙ በመቅረታቸው ምክንያት ለጊዜው እስከሚያዙ ድረስ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ እና 11ኛ ተከሳሾች ክሳቸው ለጊዜው እንዲቋረጥ በፍርድ ቤቱ ብይን መሰጠቱ ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.