Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታትና ለመበተን የተወሰነ ውሳኔ የለም- ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የተወሰነ ውሳኔ የለም ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
 
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
 
በመግለጫቸውም÷በሀገር ደረጃ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ለማደራጀት መወሰኑን ተናግረዋል፤ወደ ትግበራም መገባቱን ገልፀዋል።
 
ውሳኔው በፌዴራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት ስምምነት የተወሰነ መሆኑን ጠቁመው÷ ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነም አንስተዋል።
 
በአማራ ክልልም ውሳኔውን ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል፤ በአፈጻጸም ላይ በታየ ክፍተት እና በተነዛው ፕሮፖጋንዳ ችግሮች መከሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
 
ችግር እንኳን ቢኖር ተወያይቶ መፍታት ይቻላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አብዛኛው የልዩ ኃይል አባል ውይይቱን አጠናቆ ውሳኔውን በካምፕ ሆኖ እየተጠባበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
 
ጀግና ልዩ ኃይል ነው፤ መስዋዕትነት የከፈለ ልዩ ኃይል ነው፤ የአማራ ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሆኖ የሀገርን ሕልውና እና ሉዓላዊነት የጠበቀና ያስከበረ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
 
ይህ ልዩ ኃይል ትጥቅ የሚፈታና የሚበተን አይደለም፤በላቀ አደረጃጃት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡ ልዩ ኃይሉ ዓላማውን ተገንዝቦ ለበለጠ ተልእኮ እንዲዘጋጅም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የአማራ ሕዝብ በሁኔታው ቅሬታ ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ቅሬታው የመነጨው በተሟላ መንገድ ለሕዝቡ መረጃ ባለመድረሱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
 
ዓላማው የሀገር አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያስቀጥል እና የጸጥታ መዋቅሩ በክልልም ሆነ በፌዴራል የተናበበና ሕግን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ማድረግ ነውም ብለዋል፡፡
 
አደረጃጀቱ የሚደገፍ፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የሀገርን አንድነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸው÷ አደረጃጀቱ የአማራን ክልል በተለየ መንገድ የሚጎዳ አይደለም ብለዋል፡፡
 
የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የታለመ ዓላማ እንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡
 
በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት በአንዳንድ ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ፣ የአድማ ጥሪ እና የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን የመገደብ አዝማሚያዎች እያታዩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
 
አላስፈላጊ አካሄዶች አውዳሚ እና አክሳሪ እንጂ አትራፊ አለመሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
የአማራ ክልል በጦርነት የከረመ ክልል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በጦርነቱ ምክንያት ሕዝቡ ተጎሳቁሏል፣ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳው ኅብረተሰብ እና መሠረተ ልማት ገና ማገገም አልቻለም ብለዋል፡፡ ከአንደኛው ችግር ሳናገግም ወደ ሌላ ችግር መሸጋገር ሕዝቡን መጉዳት ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
 
በመወያየት አላስፈላጊ ጉዳዮችን ማስቆም እንደሚቻልም ገልጸው÷ ሁሉም አውዳሚ የሆነውን ጉዳይ መከላከል እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡
 
ግጭት እንዳይፈጠር ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶች የሚመሰገን ሥራ እየሠሩ መሆናቸውንም ነው ያወሱት፡፡
 
የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን በውል በማጤን፣ በመመካከር እና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ በማሰብ መስከን ይገባልም ብለዋል፡፡
 
የአማራ ልዩ ኃይል በተለየ መንገድ የሚጎዳ ውሳኔ አልተወሰነም፤ ወጥና ሀገራዊ ውሳኔ ነው የተደረገው፤ በሁሉም ክልል የሚፈጸም ነው፤ ውሳኔው ለሀገር ግንባታ ታላቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው እናምናለንም ብለዋል፡፡
 
ከወቅታዊ ጉዳይ አንጻር የሚነሳው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም አፈጻጸሙ ለሀገር የሚጠቅም መሆኑን መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ከካምፕ የወጡ የልዩ ኃይል አባላት እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
 
በረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪኩ እና በስርዓት አክባሪነቱ የሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማየት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ችግሩ ዳር ወጥቶ ግጭት እንዳይከሰት እያደረጉ ላሉ አካላትም ምስጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
 
የልዩ ኃይል አባላት ትጥቅ አትፈቱም፣ የምትበተኑበት ነገር የለም፣ ወደ ላቀ ተልእኮ ነው የምትሽጋገሩት፣ ይሄን አውቃችሁ ለሀገራችሁ እና ለክልላችሁ ስታደርጉት የነበረውን አስተዋጽዖ በተሟላ መንገድ ለማስቀጠል እንድትችሉና እንድትዘጋጁ አደራ እላለሁም ብለዋል፡፡
 
በመደማመጥ ችግሮቻችን እንፈታለን፣ የአማራን ጥያቄዎች እናስመልሳለንም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.