Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በመዲናዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

በዚህም በህዝብ ጥያቄ የተጀመሩ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን፣ የከተማዋ የግብርና ምርት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ወሳኝ ሚና ያላቸው የገበያ ማዕከላትን፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለምርት አቅርቦት ትልቅ ሚና ያለው የኢንዱስትሪ ክላስተርን ጎብኝተዋል፡፡

በተጨማሪም የመንገድ ፕሮጀክቶችን፣ የአመራሮችን ብቃት ለመገንባት የሚያግዝ አካዳሚን ጨምሮ የሌሎች ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙት የእነዚህ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

መጀመር ብቻ ሳይሆን በጊዜ የማጠናቅቅ ልማዳችንን በማጠናከር ፕሮጀክቶቻችን በተያዘላቸው ጊዜ እና በተመደበላቸው በጀት በጥራት ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፉ፣ የህዝቡን የኑሮ ሸክም የሚያቀሉ፣ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ የሚያሻሽሉ መሆናቸውንም ጠቁዋል፡፡

በመዲናዋ በታማኝነት እና በትጋት ለማገልገል የተገባው ቃል በተግባር እንዲፈጸም የበኩላቸውን ለተወጡ ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.