ሚኒስቴሩ ለ2 ሺህ 800 ዐቅመ-ደካማ የከተማዋ ነዋሪዎች ማዕድ አጋራ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የዓብይ እና የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ ለ2 ሺህ 800 ዐቅመ-ደካማ የከተማዋ ነዋሪዎች ማዕድ አጋራ፡፡
ከ420 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብሩን ያከናወነው በባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ከታቀፉ ዐቅመ-ደካሞችና አረጋውያን ጋር ነው፡፡
በማዕድ ማጋራቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፋት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ÷ ይህ ዓይነቱ ተግባር ያለንን የእርስ በእርስ መደጋገፍና መፈቃቀር የሚያጎለብት ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሰል ተግባር ላይ ለተሰማሩ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የማዕድ ማጋራቱ የተካሄደበት ባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት ከ3 ሺህ 800 በላይ ዐቅመ-ደካሞችን በቋሚነት እየመገበ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡
ላለፉት አራት ዓመታትም በሥሩ ላቀፋቸው ዐቅመ-ደካሞች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በቤተልሔም መኳንንት