Fana: At a Speed of Life!

አፍራሽ አጀንዳዎችን ለመመከት የፌዴራል እና የክልል ኮሙኒኬሽኖች በጋራ ሊሰሩ ይገባል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍራሽ አጀንዳዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመመከት በፌዴራል እና በክልል የኮሙኒኬሽን ስራዎች በመናበብ ሊሰሩ እንደሚገባ የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኮሙኒኬሽን ሥራዎቻችን የበላይነትን ይዘው እንዲቆዩ የመንግስትን ዋና ዋና አጀንዳዎች በሚገባ መለየትና በእቅድ አካቶ መስራት ይገባል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

በአዳማ እየተካሄደ በሚገኘው “ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና” የስልጠና መርሐ ግብር ላይ “የሕዝብ ግንኙነትና መሰረቶች፣ አጀንዳ ቀረጻና የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን” በሚል ርዕስ የስልጠና ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ከሃገራዊ አበይት እቅዶች ጋር በማጣጣም የኮሙኒኬሽን አጀንዳን በጥናት ላይ ተመስርቶ መምረጥ፣ ፈተናዎቹን መለየት እንዲሁም በአጀንዳው ላይ የሚሳተፉ አካላትን ማንነትና ድርሻቸውን ማመላከት ከዘርፉ ባለሙያዎች ይጠበቃል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

የፖለቲካ አጀንዳ ባለቤት መንግስት እንደመሆኑ ይህንን ለውጤት ለማብቃት በተሟላ ግንዛቤ የመሪነት ሚናን መጫወት፥ እያንዳንዱን የኮሙኒኬሽን ስራም ከትላልቆቹ ሃገራዊ አጀንዳዎች ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የመንግስት አጀንዳዎች የበላይ እንዳይሆኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸውም አንስተዋል፡፡

በተለይ የታቀዱ አፍራሽ አጀንዳዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመመከት በየክልሉና በተቋማት የሚገኙ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በእቅድ፣ በተግባርና በመልዕክት መናበብ እንደሚገባም አውስተዋል።

የኮሙኒኬሸን ሥራ በስትራቴጂካዊ የኮሙኒኬሽን ዕቅድ ሊመራና የዘርፉ ባለሙያዎች ከሚዲያ ጋር መልካም ግንኙነትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ለክልልና ለተቋማት የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊዎችና ለሚዲያ አመራሮች እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና የሚዲያ አመራርና ለህዝብ የሚቀርቡ ንግግሮች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ የስልጠና ሰነዶች ለኮሙኒኬሽን ባለሙያዎቹ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.