ስፓርት

በፕሪሚየር ሊጉ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ድል ቀንቷቸዋል

By Mikias Ayele

April 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ቀን 9 ሰዓት ላይ ከሀድያ ሆሳዕናን ጋር የተጫወቱት ድሬዳዋ ከተማ ከመመራት ተነስተው ከዕረፍት መልስ ቢኒያም ጌታቸው እና አቤል አሰበ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2 ለ 1 አሸንፈዋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎም በረሀማዎቹ ነጥባቸውን 24 በማድረስ ከአዳማ ከተማ ጋር እኩል 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችሉ ሀዲያ ሆሳዕና በነበረበት 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የተጫወተው ኢትዮጵያ መድን ከግማሽ ደርዘን ጎል ላይ አስቆጥሮ 7 ለ 1 አሸንፏል፡፡

ካርሎስ ዳምጠው የለገጣፎን ብቸኛ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡

ለመድን ሲሞን ፒተርስ እና ኪቲካ ጀማ ሁለት ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ፥ ሀቢብ ከማል፣ ብሩክ ሙሉጌታ እና ወገኔ ገዛኸኝ በስማቸው አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል፡፡

ውጤቱን ተክትሎ ኢትዮጵያ መድን በእኩል 36 ነጥብ በመያዝ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ማጥበብ ችሏል፡፡