የነገው የቡድን 7 አባል ሀገራት ስብሰባ በዋጋ ግሽበት እና በዩክሬን ጉዳይ ላይ ይመክራል
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ነገ በአሜሪካ የሚጀመረው የቡድን 7 አባል ሀገራት ስብሰባ በዋናነት በዋጋ ግሽበት እና በዩክሬን ጉዳይ ላይ ይመክራል ተባለ፡፡
ስብሰባውን ጃፓን በሊቀ መንበርነት እንደምትመራውም የሀገሪቷን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ሰባቱ በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሀገራት በዓለም አቀፉ የአቅርቦት ሠንሠለት ላይ እና ከሉላዊ ኢኮኖሚው ጀርባ ባሉ ጉዳዮች ላይም እንደሚወያዩ ተነግሯል፡፡
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ተብለው የሚታወቁት ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ናቸው፡፡
ከሀገራቱ ስብሰባ ጎን ለጎን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ መሪዎች ዓመታዊ የግንኙነት መርሐ-ግብር እንደሚኖራቸውም ተመላክቷል፡፡
በስብሰባው ለመካፈል የጃፓን የገንዘብ ሚኒስትር ሹኒቺ ሱዙኪ ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙ ተጠቁሟል፡፡