Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በኃይሉ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ያላትን ፍላጎት ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በኃይሉ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ያላትን ፍላጎት ገልጻለች፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ከኢፌዴሪ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የሩሲያ መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጋር የቆየ ጠንካራ ወዳጅነት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ኢንጂነር ሐብታሙ ÷ሩሲያ በልማቱ መስክም በኢትዮጵያ የመልካ ዋከና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ አስታውሰዋል፡፡

የሩሲያ ድርጅቶች በኢነርጂ አቅርቦት ላይ  መሰማራት የሚችሉባቸውን መስኮችም አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ዐቅም ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸው ምሥራቅ አፍሪካን በኃይል ለማስተሳሰር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው ÷ በሩሲያ ትልቁ የኃይል አቅራቢ ድርጅት የሆነው ሩስ-ኃይድሮ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ላይ መሳተፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም በጉዳዩ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና እንዲሁም የዘርፉ ተቋማት አመራሮች ከድርጅቱ አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ እንደሚመክሩ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.