Fana: At a Speed of Life!

የልዩ ኀይል ሪፎርም የሚካሄደው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የሀገርን አንድነት የሚያጸና ጠንካራ የጸጥታ ኀይል ለመገንባት ነው- አቶ ግርማ የሺጥላ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ልዩ ኀይል መከላከያ ሠራዊት በተከዳበትና ሀገር ኅልውናዋ አደጋ ውስጥ በገባበት ወቅት መስዋእትነት የከፈለ መኾኑን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ አስታውቀዋል።

አቶ ግርማ የልዩ ኀይል ሪፎርም የሚካሄደው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የሀገርን አንድነት የሚያጸና ጠንካራ የጸጥታ ኀይል ለመገንባት ነው ብለዋል።

የልዩ ኀይል ሪፎርምን ተከትሎ በአማራ ክልል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያታቸው ጉዳዩን በሚመለከት የግንዛቤ ሥራ በአግባቡ ባለመሠራቱ ነው ብለዋል።

የክልል ልዩ ኀይሎችን ሪፎርም የማድረጉ ጉዳይ የቆየ ውሳኔ ነው ያሉት አቶ ግርማ፤ በሰሜኑ ግጭት ምክንያት ተግባሩ መዘግየቱን አብራርተዋል።

በክልሉ መከላከያ ሠራዊት ሲንቀሳቀስ ሌላ ኀይል እንደገባ ተደርጎ የሚሠራጨው አጀንዳ አንድ ጠንካራና ወጥ መከላከያ ለመገንባት የሚደረገውን ሂደት የሚጎዳ እንደሆነም ገልጸዋል። ወደ አማራ ክልል ምንም አይነት የተለየ ኀይል እንዳልገባም አረጋግጠዋል።

የአማራ ሕዝብ የደረሰበትን መፈናቀል፣ ሞት እና አለመረጋጋት የክልሉ መንግሥትና ብልጽግና ፓርቲ በልዩ ትኩረት ችግሩን ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም ከክልሉ መሪዎች እውቅና ውጭ ከልዩ ኀይል ሪፎርም ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያ ልዩ ኀይሉ ትጥቅ እንደሚፈታ ተደርጎ የተሠራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን አስገንዝበዋል

በሪፎረሙ ትጥቅ ስለመፍታት የተላለፈ ውሳኔ እንደሌለም አረጋግጠዋል። በቀጣይም በሰከነ መንገድ በጉዳዩ ላይ በመወያየት የመልሶ ማደራጀት ተግባሩ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እንደሀገር አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋታል ያሉት አቶ ግርማ ይህንን ለማሳካትም የአማራ ክልል በትልቅ ኀላፊነት እየሠራ ነው ብለዋል።

የአማራ ልዩ ኀይል በክልሉ ሕዝብና መንግሥት ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበታል ይህ ኀይልም ፖለቲካዊ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ይልቁንስ የሀገርና የሕዝብ አለኝታነቱን ይበልጥ የሚያሳይበትን አደረጃጀት ተከትሎ እንዲደራጅ ይደረጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል በጦርነት ውስጥ የቆየ ነው፤ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ እነዚህ ተስፋ ሰጭ ሥራዎችም መሰናከል የለባቸውም ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

መንግሥት ሁሉንም ነገር በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ግርማ፤ በዚህ ወቅት በመደማመጥ ችግሮችን በመፍታት ለአማራ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም መሆኑን አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.