Fana: At a Speed of Life!

በበዓል ሰሞን አደጋ እንዳይከሰት ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከበዓላት ጋር በተያያዘ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

በበዓላት ወቅት እሳት እና የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ይህን ተከትሎ በመጪው የትንሳዔ በዓል የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የትንሳዔ በዓል ዝግጅቶች በአብዛኛውን ምሽት ላይ ስለሚከናወኑ መዘናጋትና ድካም ሳይኖር ሥራዎችን በንቃት እና በአግባቡ ማከናወን እንደሚገባ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ መክረዋል፡፡

ሁሉንም ስራዎች በአንድ ጊዜ ለማከናወን የሚደረግ ጥረት ትኩረትን በማሳጣት ለድካም ብሎም ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ስራዎችን በቅደም ተከተል ማከናወን እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

እንዲሁም ከሰል እንደ ኃይል አማራጭ ጥቅም ላይ ሲውል በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው÷ በሌሊት የሚበስሉ ምግቦችን ጥዶ መተኛት አደገኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ቀደም ሲልም በርካቶች በዚሁ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን ነው ያስታወሱት፡፡

በተጨማሪም ሻማ ለኩሶ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሄድ ለአደጋ ስለሚዳርግ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ አደጋዎች እንዳያጋጥሙ በአደጋ ቅነሳ ዘርፍ በተመረጡ የገበያ ስፍራዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አላፎ አደጋ ቢከሰት አደጋውን ለመቆጣጠር በኮሚሽኑ በዘጠኙም የቅርጫፍ ጣቢያዎችና በማዕከል የአደጋ መቆጣጠር ማሽነሪዎች ፣ የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኞችና የአንቡላንስ አገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ማሕበረሰቡ የትንሳኤ በዓል ያለምንም አደጋ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበው አደጋ ከተከሰተ በ939 ወይም በ0111555300 በመደወል እንዲያሳውቅ ተጠይቋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.