Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በተመድ የሕዝብና ዕድገት ኮሚሽን ጉባዔ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው በተባበሩት መንግስታት የሕዝብና ዕድገት ኮሚሽን 56ተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡

ጉባዔው “ሕዝብ፣ ትምህርት እና ዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሔደ የሚገኘው፡፡

በፕላንና ልማት ሚንስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ የተመራ ልዑክ በመድረኩ  መሳተፉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኝ መሆኗን እና  ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ሰፊውን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ አቶ ሳንዶካን በመድኩ ላይ ገልፀዋል፡፡

የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት ሀገራዊ የሕዝብ ዕድገትን ከዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ማስተሳሰር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ስመሆኑም አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሥነ ሕዝብና የሕዝብ ቁጥር የዕድገት ምንጭ የሚሆንበት፣ የውልደት ምጣኔ በተዋልዶ ትምህርት እና ግንዛቤ ላይ የተገነባ እንዲሆን በተሠራው ሥራ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም በትምህርትና ጤና ዘርፍ ሰፊ ኢንቨስትመንት በማከናወን የዘላቂ ልማት ግቦችን በጠንካራ መሰረት ላይ የለመጣል እየተሠራ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

ስለሆነም ጥራት ያለው የትምህርት አቅርቦትን ለማረጋገጥ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍና ቅንጅታዊ ስራ እንደሚስልግ ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.